የጥንት ኢትዮጵያዉያንን ምጡቅ የአሳሳል ክህሎትና ቅርሶችን ማንሰራራትና ለቀጣይ ትዉልድ ማስተላለፍ
የህዝቅኤል መንገድ
በጌርዳ ሄንከል ፋውንዴሽን የፓትሪሞኒ የገንዘብ ድጋፍ ተነሳሽነት የተመሰረተ ፕሮጀክት።
ባህልና ቅርስ ኢትዮጵያ የምትኮራባቸውና፣ የምትጠብቃቸው፤ ለህልውናዋም ወሳኝ አድርጋ የምትቅጥራቸው ሃብቶቿ ናቸው።
ለዚህ ፕሮጀክት ጥንሥስ መነሻ የሆነንም በ18ኛው ክፍለ ዘመን ሕዝቅኤል በሚባል ሊቅ የተሳሉና በግእዝ የተጻፉ በመዝገብ ቁጥር Or. 790 እና Or 791 ተብለዉ በብሪቲሽ ላይብረሪ (ለንደን) በቅርስነት የተቀመጡ ሁለት ጥራዝ የሃዲስና የብሉይ ኪዳን የብራና መጽሃፍ ቅዱሳት ናቸው። ሁለቱ መጻሕፍት በዉስጣቸው 729 የሚያህሉ ድንክዬ (miniature) ስዕሎች ይዘዋል። ሰዓሊው ሕዝቅኤል የሚባል ኢትዮጵያዊ መሆኑ የታወቀውም በእያንዳንዱ ጥራዞች ውስጥ በአንድ ነጠላ ኮሎፎን ላይ (በመፅሀፍ ገፅ መጨረሻ የሚፃፍ) በማን እንደተሳለ የሚገልፅ ስም ስላለ ነው።

የስራዎቹ የበለጸገና ወጥ የሆነ የመስመር፣ የቅርጽ፣ የምልክት፣ የቅንብር፣ የብሩሽ ዱካ እና ውብ የቀለም አቀማመጥ ያላቸው ሲሆን የሕዝቅኤልን ምጡቅ የአሳሳል ዘይቤ ያሳዩናል። ሁለቱ መጻሕፍት በትክክል ተጠርዘው እና ጽሑፎቹ ሙሉ በሙሉ ተፅፈው ሳለ፣ እኛ አሁን በማናውቀው ምክንያት፣ በመፅሃፍቱ ውስጥ ከተሳሉት ከግማሽ በታች የሚያህሉት ስዕላት ቀለም ያልተቀቡና በንድፍ ደረጃ ብቻ የቀሩ ናቸው። ይህም ማለት እነዚህ በንድፍ ደረጃ ያሉ ስዕላት በሞኖክሮም መስመር ስዕሎች ደረጃ ብቻ ቀርተዋል ማለት ነው ። ሌሎች 39 ደግሞ በከፊል ቀለም ብቻ ቀርተዋል። እነዚህ ድንክዬ ስዕሎች በሙሉ ገፅታቸው ምን እንደሚመስሉ ለማዬት ባለመታደላችን እናዝናለን። ነገር ግን የሕዝቅኤልን ልዩ ተሰጥዖና የአሳሳል ጥበብ፤ ስራዉንና ሃሳቡን ለመረዳት እድል ይሰጡናል።
የፕሮጀክት ቡድናችን የህዝቅኤልን የስዕል አሳሳል ዘዴ ለመረዳት እና ለመተንተን ይሰራል። ይህንንም ዘዴ ዳግም ለማንሰራራት በተለያዩ ጠቃሚ በሆኑ መንገዶች እናቀርባለን:: ከእነኝህም መንገዶች መካከል፤
1ኛ) የህዝቅኤልን የአሳሳል ዘዴ በማጥናት ስእሎቹን እንደገና በኮምፑተር ዳታቤዝ በማስገባት፤ የማስተማሪያ መርጃ መጽሃፍትን በማዘጋጀት፣ በሐመረ ብረሃን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የብራና ሥዕል ትምህርት ቤት ስለ ህዝቅኤል አሳሳል ኮርሶችን በማዘጋጀትና በማስተማር
2ተኛ) ስለ የሕዝቅኤል የአሳሳል ጥበብና ስለ ሁለቱ መጻህፍት የሚያትት መፅሀፍ በማዘጋጀት ይሰራል። የተሰሩትን ስራዎችም የተለያዩ ዓውደ ርዕሮች በማዘጋጀት ለህዝብ ማቅረብ ይሆናል።
ቅርስ እንክብካቤ እና ጥበቃ የሚያስፈልገው የሚዳሰስ ቁስ ብቻ ነው ብለን አናምንም። ነገር ግን ህያው ሆኖ የሚኖር ይዘትና የማይዳሰስ ቅርጽም አለው። ስለሆነም ያለፈዉንና የጥንቱን በማንሰራራትና ዛሬም ህያው ሆነው ለቀጣይ ትውልድ እንዲቀጥሉ ለሚደረገው ጥረት እኛም የበኩላችንን አስተዋፅኦ ለማበርከት እንፈልጋለን። አንድ ህዝብ ባለፈው ስራው ብቻ ሳይሆን የሚለካው በቀጣይነት በሚያከናውነውም ስራ ጭምር መሆኑ የማይካድ ሃቅ ነው። ለዚህም ይህ ፕሮጀክት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።
የፕሮጀክቱ አባላት
ትንሳኤ ተስፋሚካኤል ሃይሉ | ዶ/ር ጌታነህ አለሙ | ገብረኢየሱስ አስማረ |


